Jump to content

ቅየሳ

ከውክፔዲያ

ቅየሳ የአንድን የመሬት ገጽ ወይም የግንባታ አካል አቀማጥ ለማወቅ የሚደረግ የልኬት ስራ ነው። የቅየሳ ስራ ለቅየሳ ስራ የሚውሉ እንደ ውሃ ልክ (level) ወይም ቴዎዶላይት ያሉ መሳሪያዎች በመጠቀም በሁለት የልኬት ቦታዎች መካከል ከልኬት ቦታው አንጻር የሚኖረውን የቦታ ልዮነት ለማወቅ የማእዘን (angle) ፣ የአግድም ቁመትና የሽቅብ ቁመት ልኬቶችን በመውሰድና የሂሳብ ስሌትን በመጠቀም የመሬት ገጽን ወይም የግንባታ አካልን አቀማመጥ የመወሰን ተግባር ነው። ከኮምፒውተር እውቀት ማደግ ጋር በተያያዘ አውቶማቲክ የሆኑ የኤሌክትሪክ ርቀት መለኪያዎች በመፈልሰፋቸው እንደ ቶታል ስቴሽን፣ ጂፒኤስ፣ የጨረር ዳሰሳ (laser scanning) የመሳሰሉ መሳሪያዎች ባህላዊ የሆኑ መሳሪያዎችን በመተካት ላይ ይገኛሉ።

የመሬት ገጽ አቀማመጥና በመሬቱ ላይ ያሉ የግንባታ አካላትን ለማወቅ በቅየሳ የተሰበሰበ መረጃ አብዛኛውን ጊዜ ወደ ስእላዊ የመሬት ካርታ ይቀየራል። ይህ ስእላዊ የመሬት ካርታ የንድፍ ስራዎችን ለማከናወንና ለመገንባት ትልቅ እገዛ ያደርጋል። ምንም እንኳን ቅየሳ ራሱን የቻለ የሙያ ዘርፍ ቢሆንም፣ ሲቪል መሃንዲሶች መሰረታዊ የቅየሳ፣ የካርታ ስራ እንዲሁም የጂኦግራፊ መረጃ አሰባሰብ ስርዓት (geographic information systems) እውቀት አላቸው። የቅየሳ ባለሙያዎች ልኬቶችን ከመውሰድ በተጨማሪ፣ የባቡር ሃዲድ፣ የመንገድና የትቦ መስመሮችን አቅጣጫ የመዘርጋትና ሌሎች የግንባታ አካላት ትክክለኛ ቦታቸውን ይዘው እንዲገነቡ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጋሉ።