Jump to content

አሙና

ከውክፔዲያ

አሙና ከ1491 እስከ 1488 ዓክልበ. ድረስ አካባቢ ከአባቱ ከ1 ዚዳንታ በኋላ በሐቱሳሽ (በሐቲ አገር ወይም የኬጥያውያን መንግሥት) የገዛ ንጉሥ ነበር።

አባቱ ዚዳንታ ዙፋኑን ከያዘ በኋላ በቅርቡ አሙና በፈንታው አባቱን ገድሎ ንጉሥነቱ ለራሱ ቃመ።

ይህን የምናውቀው ንጉሡ ቴሌፒኑ በጻፈው የቴሌፒኑ ዐዋጅ በተባለው ሰነድ ይተረካል።

«ዚዳንታም ንጉሥ ሆነ። አማልክት ስለ ፒሼኒ ደም ቂም ፈለጉ። አማልክት የገዛ ልጁ አሙና እንደ ጠላቱ አድርገው እሱም አባቱን ዚዳንታን ገደለ።
አሙናም ንጉሥ ሆነ። አማልክት ስለ ዚዳንታ ስለ አባቱ ደም ቂም ፈለጉ፣ በእጁም እሱ፣ ወይም እኅሉ፣ ወይም ወይን ጠጁ፣ ወይም በሬ ወይም በግ እንዳይበለጸጉ አደረጉ።
አገሩም ጠላት ሆነበት። ሥራዊቱ የትም ቢዘመቱ፣ ማለት ወደ ከተሞቹ [...]አጋ፣ ማቲላ፣ ጋልሚያ፣ ወይም ወደ አገራት አዳኒያአርዛዊያ፣ ወይንም ወደ ከተሞቹ ሻላፓ፣ ፓርዱዋታ፣ አሑላሻ፣ ቢዘመቱም ስኬታም ሳይሆኑ ተመለሱ። አሙናም ደግሞ አምላክ ሊሆን ሲል፣ የንጉሣዊ ዘበኞች አለቃ ዙሩ በምስጢር ከገዛ ቤተሠቡ ልጁን ታሑርዋይሊን፣ «የወርቃማው ጦር ሰውዬ» የተባለውን፣ ልኮ እርሱ የቲቲያን (የአሙና በኲር) ቤተሠብ ከነልጆቹ ገደላቸው።
መልእክተኛውንም ታሩሕሹን ልኮ እርሱ ሐንቲሊን (የአሙና ፪ኛ ልጅ) ከነልጆቹ ገደላቸው። ሑዚያም ንጉሥ ሆነ...»

በዚሁ ታሪክ፣ ዙሩ «የንጉሥ ዘበኞች አለቃ» ሲባል ይህ ማዕረግ ለንጉሥ ወንድም እንደ ተሰጠና ዙሩ ታዲያ የአሙና ወንድምና የዚዳንታ ልጅ እንደ ነበር ይታመናል። ልጁም ታርሑዋይሊ «የወርቃማው ጦር ሰውዬ» ደግሞ ወደፊት ንጉሥ ሆነ። ዙሩ ቀዳሚ ወራሾቹን ቲቲያንና ሐንቲሊን ያስገደላቸው ለአሙና ሦስተኛው ልጅ 1 ሑዚያ ወራሽነት እንዲያገኝ እንደ ነበር ይታስባል።

በአሙናም ዘመን ጎረቤት አገራት ኪዙዋትና (አዳኒያ፣ ወደፊትም ኪልቅያ) በደቡብ ምሥራቅ፣ እና አርዛዋ በምዕራብ፣ ከኬጥያውያን ነጻ እንደ ወጡ ይመስላል። አሙና ደግሞ ከአንድ ዜና መዋዕል ጽላት ፍርስራሾች ይታወቃል። በዚህ ዘንደ የቀድሞ ዋና ከተማ ካነሽ ካመጸበት በኋላ ያዘው፣ በቅርብም ግን እንደገና አመጸ። እንዲሁም በሻቲዋራ፣ በሑላና ወንዝ አገር፣ እና በሹሉኪ ላይ እንደ ዘመተ ይላል። ዛልፓቡሩሻንዳ በአሙና ወገን እንደ ቀሩ ይመስላል።

በተጨማሪ «የአሙና መጥረቢያ» ከተባለው ቅርስ ይታወቃል። በዚህ ላይ «ታባርናው አሙና ታላቅ ንጉሥ ነው። የዚህን ቃል ዕውነት የሚቀይር ይሞታል» በኬጥኛ ተጽፎ ተቀረጸ።

ቀዳሚው
1 ዚዳንታ
ሐቲ ንጉሥ
1491-1488 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
1 ሑዚያ